በአዲስ አበባ የቤት ግብር /House property tax in Addis Ababa

በአዲስ አበባ የቤት ግብር ከሚከፍሉ 183 ሺህ ገደማ መኖሪያ ቤቶች የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ፤ 47.7 ሚሊዮን ብር መሆኑን ከከተማይቱ ፋይናንስ ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ግብር ከሚከፈልባቸው ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ 12 በመቶው የሚከፍሉት “ከ10 ብር በታች” መሆኑን የሚገልጹት በአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ የንብረት ታክስ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አስማማው ሙሉጌታ፤ 46 በመቶው ደግሞ “ከመቶ ብር በታች” መሆኑን በአጽንኦት ጠቅሰዋል። 2,500 ያህል ቤቶች ከ1 ብር በታች እንደሚከፍሉ በተጨማሪነት ያነሱት አስተባባሪው፤ “ለዓመታዊ ግብር ከ1 ብር በታች ማለት በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው። አሁን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ምክንያታዊም አይደለም” ሲሉ አሁን የተደረገውን ማሻሻያው አስፈላጊነት አስገንዝበዋል።

የፌደራል መንግስት የንብረት ታክስ (property tax) አዋጅ ገና እያዘጋጀ ቢሆንም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን እስከዚያው ድረስ በቀድሞው አዋጅ ላይ ተመስርቶ ከቤት ግብር የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጥናት ማድረጉን አስተባባሪው ገልጸዋል። በዚህ ጥናት በአዲስ አበባ የሚገኙ ቤቶች በቦታ ደረጃቸው፣ በተገነቡበት ቁስ እና በአገልግሎት አይነታቸው ተከፋፍለው፤ አዲስ ወርሃዊ የኪራይ ዋጋ እንደተተመነላቸው አቶ አስማማው አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ የፋይናንስ ቢሮ ባለፈው ሚያዝያ ወር ባወጣው “የጥናት ውጤት ውሳኔ” መሰረት፤ ቤቶች ያረፉባቸውን ቦታዎች ታሳቢ በማድረግ በአራት የተለያዩ ደረጃዎች ይከፋፈላሉ። በጥናቱ ከፍ ያለ የኪራይ ዋጋ ተመን የተገመተላቸው “ደረጃ አንድ” ላይ የሚመደቡ ቦታዎች፤ ከዋና መስመር ያላቸው ርቀት እና የተሟላላቸው መሰረተ ልማት ታሳቢ ተደርጎላቸዋል።

Scroll to Top